Friday, February 26, 2010

የቤተ ክርስትያናችን ችግር!!!

በአቶ ኢዮኤል ነጋና በአቶ ጌታቸው ትርፌ የበላይ አቀነባባሪነት የሚንቀሳቀሰው ቡድን ምርጫዉን አክብሮ መቀበል አቅቶታል። እነዚህ ቡድኖች ነጻ አገልግሎት የሚስጥበትን ስራ ላለመልቀቅ ህዝብን ግራ አስቲገባው ድረስ ሙጥኝ ብለው የሚታገሉት ለምን ይሆን? በተከታዮቻቸው አማካኝነት ዶክተር ግርማና አቶ አበራ የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ ለመዝረፍ ሲሉ በጦር መሳርያ ሃይል ተደግፈው ኩዴታ ፈጥረው ራሳቸውን ቦርድ ብለው የሰየሙ ሰዎች ናቸው ብለው ሊያሳምኑን እየሞከሩ ነው።

ቤተክርስቲያናችን ችግር ውስጥ የገባችው በነዚህ ሁለት ግለሰቦች ምክንያት ነው ብላችሁ እመኑ እያሉን ነው። ተረት ተረቱን ለነሱ እንተወውና እነዚህ ግለሰቦች ቦርድ ውስጥ የገቡት መች ይሆን? ሁላችሁም እንደምታስታውሱት March 2008 ላይ ነው።
በዚህ ወቅት በተደረገው ምርጫ፦
1 አቶ ኢዮኤል ነጋ (በተከታታይ ቤተ ክርስትያን ከተመሰረተ ጀምሮ)
2 አቶ አበራ ፊጣ ለመጀመርያ ጊዜ
3 ዶ/ር ግርማ ወ/ሩፋኤል ለመጀምርያ ጊዜ በምእመናን ተመርጠው የቦርድ አባላት ሆኑ።

ሥራ ከጀመሩ በኋላ በተለይ ሁለቱ አባላት ቤተክርስትያናችን የገንዘብ አያያዝና የሂሳብ አሰራር ችግር እንዳለበት ሲረዱ ይሄንኑ ጉዳይ ለቦርዱ እና ለህዝብ አሳውቁ። ከዚህ ቀን ጀምሮ ለረጅም ዘመን የባከነውን ገንዘብ እና አሰራር ህዝብ አንዳይሰማና ኦዲት አንዳይደርግ አፍነው ለመያዝ ሙከራ ተደረገ። ህዝቡንም ለማሳመን አሳሳች ኦዲተር በአቶ ጌታቸው ትርፌና በአቶ ኢዮኤል ነጋ አማካኝነት ተቀጥሮ የተዛባ ሂሳብ ለምእመኑ ቀረበ።

በሌላ አቅጣጫም ሚስጥሩን ባውጡት በነዚህ ሁለት ተመራጮች ላይ እስካሁኑ ሰዓት ድረስ የስም ማጥፋት ዘመቻ በከፍተኛ ፍጥነት እየተጧጧፈ ይገኛል። ከተቻላቸውም ሁለቱንም ከቦርድ ለማስወጣት ሙከራ በማድረግ ላይ ናቸው። የአቶ ኢዮኤል ነጋና የአቶ ጌታቸው ትርፌ ሃዘንና ሽብር መንስኤው ይሄው ከሂሳቡና ከገንዘቡ ጋር የተያያዘው ሁኔታ ነው። ሃቁ ይህ ነው፡ እነሱ ሊያሳምኑን እንደሚሞክሩት የቤተ ክርስትያናችን ችግር አነዚህ ሁለት ተመራጮች አይደሉም። ችግራችንን በደንብ ለመረዳት እንድትችሉ ካሁን ቀደም August 2009 ዓ.ም ላይ ያቀረብነውን ጽሁፍ እንድታነቡት በድጋሚ ዛሬ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

አብረን እናንብብ!!
ቤተክርስቲያናችንን ከቀበሌ የፍርድ ሸንጎ ወደ ተቀደሰ ደብር ለመለወጥ የተደረገ ጉዞ።
ቀደም ሲል የዳላስ እና አካባቢው ምእመናን በአንድ ደብር ጥላ ሥር ተሰባስቦ ያመልክ ስለነበር የአባላት ቁጥር ከፍተኛ ነበር። ከአባላቱ የሚሰበሰበውም ብር ጠርቀም ያለ ነበር። ብር አዋጡ ተብለው ሲጠየቁ በኪሳቸው ውስጥ ያለውን እርግፍ አድርገው ሲሰጡ አይተናል። የዓይን ምስክሮችም ነን። የዚህ ደብር ምዕመናን ለአብነት የሚጠቀሱ ብዙ አኩሪ ሥራዎችን ሰርተዋል። ወርቃማ ታሪክ ያለው ትልቅ ደብር ነው።ዛሬ ግን ይህ ሁሉ ተረስቶ ቤተክርስቲያናችን በውጭና በውስጥ በክስ ተወጥራ ትገኛለች።

ምዕመናን ተሰብስበው የሚያመልኩበት ሥፍራ መሆኑ ቀርቶ የቀበሌ የፍርድ ሸንጎ ካስመሰልነው ብዙ ዓመታት አስቆጥረናል። ያለው ችግር ተባብሶ እንዴት እዚህ ደረጃ ሊደረስ ቻለ? በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰባስበን ከተጠበቀው በላይ አድገን ብዙ በጎ ሥራዎች እና ዕርዳታዎችን በሰፊው ሰጠን። ይህንን ፈጣን እድገት ከዳር ሆኖ ይመለከት የነበረው ወያኔ ሁለት ዕቅዶችን አውጥቶ ዘመተብን።
ዕቅድ አንድ ፤ ደብሩን በራሱ ቁጥጥር ሥር ማዋል።
ዕቅድ ሁለት ፤ ይህ ካልተሳካ ምዕመኑን መበተን እና ሀይሉን መስበር ናቸው።

እነዚህን ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ የዛሬ ስድስት ዓመት በተደረገው የቦርድ ምርጫ አባ ጳውሎስ እና ወያኔ በማህበረ ቅዱሳን አማካኝነት የቦርድ አባላትን አስመረጡ። ለረጅም ዘመን ምዕመናኑ ለልጆቻችን አስተማሪ ይቀጠርልን ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ የተቀበለ በማስመሰል በወቅቱ የነበረው ቦርድ የማህበረ ቅዱሳን መሪ የሆነውን ግለሰብ የቅዱስ ያሬድ ት/ቤት አስተባባሪ (ኮኦርዲኔተር) ብሎ ከቀጠረ በኋላ ሕዝቡ ሳያውቅ በስውር “የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ” የሚል ሹመት ሰጡት።
በወቅቱ የነበሩት ርዕሰ ደብር ሞገስ እጅጉ እና መምህር ሰብስቤ ውሳኔው የነርሱን የሹመት ተዋረድ የሚጋፋ መሆኑን ሲረዱ ማህበረ ቅዱሳንን የሚቃውሙ መዘምራንን እና ምዕመናንን አሰባስበው መቅደስ ላይ በፈጠሩት እውከት ደብራችን ለሁለት ተከፈለ። ውስጥ ውስጡን በቀሳውስቱ፣ በማህበረ ቅዱሳን እና በተመራጭ የቦርድ አባላት መካከል ታምቆ የቆየው ቅራኔ ጊዜውን ጠብቆ ፈነዳ። ቤተክርስቲያናችን ችግር ላይ መውደቅዋም ይፋ ወጣ።

ርዕሰ ደብር በስማቸው ቀደም ብለው የቤተክርስቲያን ፍቃድ አውጥተው ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ስንረዳ ምዕመናን አዘንን፣ ተቆጣን። ከመቶ ሰላሳ በላይ የምንሆን ምዕመናን ተሰብስበን ድርጊታቸውን አወገዝን፣የመረጥነውንም ቦርድ መደገፍ እንዳለብን ተስማማን፤ በውስጣቸው አለመግባባትና ችግር ካለ ጉዳዩ በሥነ ሥርዓት መታየት አለበት እንጂ መቅደስ ላይ ሁከትን መፍጠር መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ገልፀን ለቦርዱ የድጋፍ ደብዳቤ አስገባን። ሌቦች ናችሁ፣ የቤተክርስቲያን ብር አባክናችኋል፤ ከሥልጣን መውረድ አለባችሁ ተበለው ማጣፊያው አጥሮአቸው የነበሩትን የወቅቱን የቦርድ አባላት አረጋግተን ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አደረግን።

ቦርድና ማህበረ ቅዱሳን ብር እያባከኑ ነው ብለው የተቃወሙ ወገኖች ራሳቸውን ከርዕሰ ደብር ለይተው ጥያቄአቸውን ማስረዳት ስለተሳናቸው ከቤተክርስቲያን ሲወጡ፤ በወቅቱ ውስጥ ለውስጥ ታምቆ የነበረውን ችግር በቅጡ ያልተረዳነው ወገኖች ቦርዱን አጠናክረን ከማህበረ ቅዱሳን ጋር እዚሁ ቤተክርስቲያን ቀረን። ማህበረ ቅዱሳንም መድረኩን ተቆጣጥሮ ብቻውን በግላጭ መጋለብ ያዘ። የበጎ አድራጎትን ገንዘብ እንዳለ ተቆጣጠረ። ለድርጅቱ ፕሮጄክቶች ሥራ ማስፈጸሚያ ብር እንደፈለገ ያወጣ ጀመር፤ ታዋቂ መምህሮቻቸውን በየሦስት ወሩ ጉባኤ በሚል ሽፋን ወደ ዳላስ ማጉረፍ ጀመሩ። Video እና CD ቀርጸው ለአለም ማሰራጨት ጀመሩ። ለጉባኤ ከአዲስ አበባ ድረስ መምህራኖቻቸውን ማስመጣትን ሥራዬ ብለው ተያያዙ። ይህ ሁሉ የሚሠራው በደብራችን ገንዘብ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ በዚያኑ ሰሞን ባስቀጠሯቸው ካህናቸው በኩል ያለቁርባን ጋብቻ እንደማይፈፀም አወጁ፤ ቀደም ብለን የተጋባነውንም ምዕመናን ዝሙተኞች መሆናችንን ማስተማር በሰፊው ተያያዙ። ይህንን ለመቋቋም ስንንቀሳቀስ ከማህበረ ቅዱሳን ጋር ግጭት ተፈጠረ። ይህንን አክራሪ ጥያቄያቸውንም እንዲያነሱ ተወሰነ።

በሌላ በኩል የቤተክርስቲያን ሕግ ማሻሻያ (Amendment) አጥንታችሁ አቅርቡ ተብለው የተመረጡ ወገኖች፤ ሕጉን እንዳለ ለውጠው አዲስ ሕግ ይዘው ብቅ አሉ። ከነሱም ጋር ፍጥጫው ቀጠለ። ተንኮላቸውም ተኮላሸ። የቦርድ አባላት ምርጫ ጊዜው ደርሶ ሲካሄድ፣ በማህበረ ቅዱሳን ቁጥጥር ሥር የነበረውን ቦርድ መለወጥ እንዳለብን አምነን ተነሳን። በተለይ ሁለተኛው ዙር የቦርድ ምርጫ ከተደረገ በኋላ ማህበረ ቅዱሳን አድማ መምታትን ተቀዳሚ ሥራቸው አደረጉት። የቤተክርስቲያኑን ንዑሳን ኮሚቴዎች እኛ ካልተቆጣጠርን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም አሉ። የደረሱበት፣ ያዩት፣ የነኩት በሙሉ የራሳቸው ይመስላቸው ጀመር። በየቦታው ችግር መፍጠርን ሥራዬ ብለው ተያያዙ። የሥም ማጥፋት ዘመቻ፣ ሐሜት፣ ውሸት፣ ነገር ፈጥሮ ማውራት፣ ማስወራት የተካኑበት እንዲያውም እነርሱ የፈጠሩት እስከሚመስል ድረስ ተራቀውበት ለማየት ችለናል።

በወጣቶችና፣ በልጆች ፕሮግራም ውስጥ ማህበረ ቅዱሳን ካልሆነ ማንም ሊሳተፍ አይችልም በማለት ሽብር መንዛት ሥራዬ ብለው ተያያዙ። እሁድ አልፎ እሁድ ሲተካ ያለማቋረጥ ረብሻቸውን አጧጧፉ። በአጠቃላይ ለቤተክርስቲያን ጉድይ ሳይሆን ጠባብ ለሆነው ለማህበራቸው ዓላማ መቆማቸውን እና ያላቸውን የዓላማ ፅናት በግልጥ በእውነት አየነው። ሆኖም ሥራቸውን እንደስማቸው ሙሉ ለሙሉ መንፈሳዊ ሆኖ አላገኘነውም። ይልቅስ በወጣትነታችን የምናውቀውን የፖለቲካ ድርጅት አስታወሱን።

ውድ ምዕመናን
ጠላቶቻችን ሊቆጣጠሩን፣ ካልሆነም ሊያፈርሱን እና ሊበታትኑን ያደረጉትን ሙከራ ከሞላ ጎደል ለመመልከት ችለናል። ለዚህ ሴራ በሩን ክፍት አድርገን ስለሰጠናቸው በዚያ ገብተው የሚፈልጉትን እየሠሩ ነው። ክፍት ሆኖ ያለው የጥፋት በርም የቤተክርስቲያኑ ልቅ የሆነና ቁጥጥር የሌለው የአስተዳደር ሥርዓት ነው። ላለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት የተጠቀምንበት የአስተዳድር ስርአት ቤተክርስቲያናችን ልትወጣው የማትችለው አዙሪት ውስጥ ጨምሮአታል። በተሰበረና በማይሠራ ሥርዓት መልሰን ለመገልገል የሚደረገው ዕርምጃ መልሶ መላልሶ ስህተት ውስጥ ይጥለናል እንጂ አንድ እርምጃ ወደፊት አይወስደንም።

እኛ የኦርቶዶክስ አማኞች የምናውቀው ሚስጥረ ቤተክርስቲያን ሰባት ነው። የደብራችን ቦርድ ግን ስምንት ሚስጥራት አሉት። ሰባቱን ሚስጥራት አባቶች አስተምረውን አበጥረን እናውቃቸዋለን። ቦርዱ የፈጠረውን ተጨማሪ ሚስጥር ግን ምዕመናን አያውቁትም። ስምንተኛው ሚስጥር የቦርዱ አባላት ተመርጠው ሥራቸውን ሲጀምሩ መቅደስ ላይ በአባቶች ተባርከው ፀሎት ተደርጎላቸው ይሰናበታሉ። ከዚያ በኋላ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በር ዘግተው መጽሐፍ ቅዱስ ጨብጠው የሚሠሩትን ሥራ፤ የሚወስኑትን ማንኛውንም ውሳኔ፤ ሠራተኛ እንዴት እንደሚቀጥሩ፤ የቤተክርስቲያን ጥገናም ሆነ የተለያዩ ወጭዎችን በተመለከተ እርስ በራሳቸው ካልሆነ በስተቀር ለማንም እንዳይነግሩ ይማማላሉ። እንግዲህ ቦርዱ ተጠሪነቱ ለመረጠው ሕዝብ መሆኑ ቀርቶ ተጠሪነታቸውን እርስ በራሳቸው አደረጉት። አሠራሩ በዚህ ዓይነት ለዘመናት የተዋቀረ ስለሆነ ደብራችን ዛሬ ያለችበት አስከፊ ችግር ውስጥ ልትወድቅ ችላለች።

በዚህ ምክንያት ይህን የመሳሰሉትን አስተዳደራዊ ችግሮችን ብንፈታ ዘላቂ ሠላምና መተማመን ይመጣል ብለን አሰብን። ግልፅ አሠራርን በቤተክርስቲያናችን ውስጥ መለማመድ አለብን ብለን ቆርጠን ተነሳን። በቅድሚያ መለወጥ ያለበት የሂሳብ አያያዝ ነው ብለን ወሰንን። ምክንያቱም ሕዝቡ ገንዘብ እንደሚባክን በይፋ መናገር ከጀመረ ቆይቶአል። የቀድሞ የቦርድ ተመራጮችን ሌቦች! ሌቦች! እያለ ያወገዘው በአደባባይ ነበር። እኛም ማህበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ ያለአግባብ ከተጠቀመባቸው መረጃዎች መካከል ጥቂቶቹን ለማየት ችለናል። ሂሳባቸውን ያላወራረዱ የቀድሞ የቦርድ አባላትን ሁሉ እናውቃለን። በ2006 ዓ/ም ቤተክርስቲያኑ ከ1.2 ሚሊዮን እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር እንደነበረው በሰማንበት ጆሮአችን 2007 ወይም 2008 ላይ ያለው ብር አሽቆልቁሎ ስምንት መቶ ሺህ ብቻ እንደተቆጠረም ተነግሮናል። በምዋቹ በአቡነ ይስሐቅ ሥም በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ውስጥ የነበረውም $450 ሺህ ብር በፍጥነት እንደተነነ ሰምተናል።

እነዚህን ሀቆች በመንተራስ አዲሱ የሂሳብ አሠራር ዘዴ ለቦርድ አባላት ቀረበ። የቀረበለትን አዲስ አሠራር መርምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ከማድረግ ፈንታ የአስተዳደር ቦርዱ ይህንን ሀሳብ በጥንስሱ ማኮላሸት ፈለገ። ቀደም ሲል ከገንዘብ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ሰብስበው የጋራ ግንባር ፈጠሩ።ይህን ሃሣብ ባቀረቡና ሃሣቡን በደገፉ የቦርድ አባላት ላይ የሥም ማጥፋት ዘመቻ አፋፋሙ። ሥማቸውን እየጠቀሱ በደረሱበት ቦታ ሁሉ የተመረጥንበትን ሥራ አላሠራ አሉን ብለው ማውራት ጀመሩ። ለስብሰባ ሲጠሩ አንመጣም እያሉ ያስቸግሩናል በማለት የሀሰት ወሬ መንዛት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆነ። ቤተክርስቲያናችን ግልፅ የሆነ አስተዳደራዊ ሥርዓት መከተል አለባት ብለን የተነሳነውን ምዕመናን የደብራችን እንቅፋትና ችግር ፈጣሪዎች ናቸው፤ ምዕመናኑን እየበጠበጡት ነው፤ መመከር አለባቸው፤ ደብሩን ችግር ላይ ጥለውታል፤ ቤተክርስቲያናችን ውድቀት ላይ ያለችው በእነዚህ ግለሰቦች እና በከሳሾች ምክንያት ነው ብለው አወሩ። መፍትሔውም ሰላምና እርቅ የሚያመጣ ኮሚቴ መፍጠር ነው ብለው ተነስተዋል። እንግዲህ ፍርዱን ለአምላክና ለእናንተ ለምዕመናን እንተወዋለን።

የቤተክርስቲያናችን የበላይ አካል አባላት ምዕመናን ናቸው። ቦርዱም ሥራውን ሪፖርት ማድረግ ያለበት ለምዕመናኑ ነው። የምዕመናኑንም ውሳኔ በሥራ ላይ ማዋል የቦርዱ ግዴታ ነው። እሩቅ ሳንሄድ በዚህ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ በተደረገው አጠቃላይ ጉባኤ የተላለፉት ውሳኔዎች ተፈጻሚነት አገኙ ወይ? ችግሩን የተለያየ ምክንያት በመፍጠር፤ ለምሳሌ፤ ፍርድ ቤት ስለተከሰስን ጌዜ ስጡን፤ ባይሎው እስከሚስተካከል ታገሱን በማለት የተመረጡበትን ሥራ በማግዋተትና የተወሰኑ ውሳኔዎችን እንክዋን በተግባር እንዳይተረጎሙና በስራ ላይ እንዳይውሉ አድርገዋል። ይህ ድርጊት ቤተክርስቲያኑን ከከሱት ግለሰቦች ይበልጥ እንደሆነ እንጂ አያንስም። ሕዝቡን ደግሞ ደጋግሞ ማሞኘት አይቻልም።

ውድ ምእመናን!!
ስለ ግልጽ አሠራር (TRANSPARENCY) ለቦርዱ ያቀረብነውን ጽሁፍ ከዚህ በፊት በድረ ገጻችን ላይ ስላወጣን እንዳነበባችሁት ተስፋ እናደርጋለን። ካላነበባችሁትም “ጁን 16, 2009 ዓ/ም ስለመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ሃሳብ” ተብሎ የተጻፈውን እንድታነቡ እንጋብዛችኋለን።
ይቀጥላል.....

No comments:

Post a Comment