Monday, October 19, 2009

ዘግይቶ የደረሰን አብይ ዜና
የቦርዱ ሊቀ መንበር በአባ ፓዉሎስ ለሚመራዉ ሲኖዶስና ለወያኔው ፓትሪያርክ ላባ ፓዉሎስ
የጻፈዉን ደብዳቤ እንድታነቡት እናቀርብላችኋለን።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ የምእመናን ማሕበር
WORLD ASSOCIATION OF PARISHIONERS OF THE ETHIOPIAN ORTHODOX TEWAHEDO CHURCH
10107 Branwood Circle, Dallas, TX 75243, U.S.A. WWW.eotcipc.org
Tel: (469)855 8488 (214)697 8928; (813)312 1502; e-mailmiimenan@yahoo.com
መስከረም 18 ቀን 2002 ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ፤
ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ
ለብፁዓን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
አዲስ አበባ።
ጉዳዩ፤ በቤተክርስቲያናችን፤ ሰላም፤ አንድነትና ዘላቂ እድገት እንዲገኝ ስለ ማድረግ፤
በመጀመሪያ፤ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ያለንን እጅግ ከፍ ያለ አክብሮት እየገለጽን፤ ለብፁዓን የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት
የእግዚአብሔር ሰላምታችንን በትሕትና እናቀርባለን።
እኛ በዓለሙ ሁሉ ተሰራጭተን የምንገኝ ተባባሪዎች የቤተክርስቲያናችን ምእመናን በቅርቡ በቅዱስ ሲኖዶሱ
አባላት መሀል በተከሰተው ውዝግብና ባጋጠሙት ድርጊቶች እጅግ ተሳቅቀናል፤ አዝነናልም። ሆኖም፤ በጥቅምት
ወር 2002 ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ስለሚከናወን ጉባኤው ለቤተክርስቲያናችን የተሙዋላ ሰላምና አንድነት
እንዲያስገኝና የዘለቄታ እድገት የሚያመቻች ስልት እንዲተልም የበኩላችንን ግንዛቤና ማሳሰቢያ ከዚህ በታች
በአክብሮት እናቀርባለን። የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤም በቤተክርስቲያናችን ላይ ተጋርጠው የሚገኙትን እጅግ ከባድ
ችግሮች ለማስወገድ ተገቢ የሆኑ መፍትሔዎችን እንደሚያስገኝ ያለንን ፅኑ ተስፋ በቅድሚያ እንገልጻለን። ስለዚህ፤
ቅዱስ ሲኖዶሱ፤ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት፤ ከዚህ በታች የምናቀርባቸውን ሀሳቦች በጥሞና ተመልክቶ ቅድስት
ቤተክርስቲያናችንን ለዘለቄታ በሚያጠናክርና በሚያስፋፋ ስልት ተገቢውን ውሳኔ እንዲያደርግ እንማጸናለን።
1. ስለ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣን፤
እንደሚታወቀው፤ በ1991 ዓ/ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተደነገገው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 5 የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣን እንደሚከተለው በግልጽ አስቀምጦታል፤
“1. በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅ/ሲኖዶስ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ
የመጨረሻው ከፍተኛው ሥልጣን ባለቤት ነው።
2. ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ሁሉ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሆነ
ሕጎችን፤ ልዩ ልዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን የማውጣትና የዳኝነት ሥልጣን አለው።”
2
ከላይ በሁለቱ ንኡስ አንቀጾች እንደተገለጸው፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን በማያሻማ ሁኔታ በግልጽ የተደነገገ ስለሆነ
በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት በወገናዊነትም ሆን በዓለማዊ ጥቅም ፍለጋ ምክንያት በማንም የውጪም ሆነ የውስጥ
አካል ተጽእኖ እንዳይሸረሸርና እንዳይዛባ በእግዚአብሔር ስም ከፍ ባለ ትሕትና እንጠይቃለን።
2. ስለ ሰላምና አንድነት፤
በአባቶቻችን መካከል የተፈጠረው አለመግባባትና መከፋፈል አደባባይ ወጥቶ መዘባበቻ በመሆኑ በአባቶቻችን ላይ
በቀላሉ የማይፋቅ ታሪካዊ ትዝብት ያተረፈላቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያናችንን እጅግ
በሚያሰጋና በሚያሳስብ ሁኔታ አደጋ ላይ ጥልዋታል። ይህ በአባቶች መካከል የተከሰተው መከፋፈል፤ መኖቆርና
አንድነት ማጣት፤ በአመራር ደረጃ የሚታየው ግዴለሽነትና ብቃት ማጣት፤ ምእመናንን ግራ ያጋባው ስደተኛ
ሲኖዶስ በመባል ያስከተለው መወጋገዝና የቤተ ክርስቲያናችን መከፋፈል አዝማሚያ መታየት እነዚህና ሌሎችም
ሁኔታዎች ለቤተ ክርስቲያናችን ጠላቶች መጠናከርና መስፋፋት አመች ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ስለዚህ የቅዱስ
ሲኖዶስ አባላት እነዚህን ለቤተ ክርስቲያናችን በጣም አደገኛ የሆኑትን ክስተቶች በማጤንና በማሰላሰል፤
በክርስቲያናዊ አስተሳሰብና ይቅር ባይነት በመካከላችሁ የተፈጠረውን አለመግባባትና መከፋፈል አስወግዳችሁ
በፍጹም ፍቅርና ሕብረት በመወያየት ቤተ ክርስቲያናችንን ከተጋረጡባት አደጋዎች እንድታድኑዋት በጌታችን፤
በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ከፍ ባለ ትሕትና እንማጸናችሁዋለን።
3. ስለ አስተዳደር ጉድለት፤
በባለሙያ የተጠና መዋቅር፤ ግልጽና የማያሻማ የአስተዳደር ደንብ፤ ዓላማው ግልጽ የሆነ የአጭር፤ የመካከለኛና
የረዥም ጊዜ እቅድ የሌለው ማንኛውም ተቁዋም፤ ብክነት፤ ሙስና፤ አድልዎ፤ የሥራ ቅልጥፍና ማጣትና
የመሳሰሉት የአስተዳደር ብልሹነት የሚታይበት መሆኑ አያጠራጥርም። ቤተ ክርስቲያናችንንም እዚህ ምስቅልቅልና
አደጋ ላይ ጥሎ ለውድቀት ከዳረጉዋት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይህ ሁኔታ መሆኑ እውነት ነው። በተለይ እንደ
ቤተ ክርስቲያናችን ያለ ግዙፍ ተቁዋም በየመስኩ በሚገኙ ባለሙያዎች የተጠና መዋቅር፤ በመዋቅሩ ላይ
የተመሠረተ ግልጽና የማያሻማ የአስተዳደር ደንብ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓላማዎች ላይ የተመሠረተ የአጭር፤
የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ጥርት ያሉ እቅዶችና በእቅዶቹ ላይ የተመሠረቱ ምእመናንንና ምእመናትን በሰፊው
የሚያሳትፉ የሥራ ፕሮግራሞች በባለሙያዎች ተጠንተው እንዲዘጋጁ ማድረግ ቤተ ክርስቲያናችንን ከውድቀት
ለማዳን አማራጭ የማይገኝለት ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ትክክለኛውን አቅጣጫ
ይዛ በመጉዋዝ እየተስፋፋችና እየተጠናከረች በመሔድ በሕገ ቤተክርስቲያናችን በአጠቃላይ የተደነገጉትን
መንፈሳዊውንና ዓለማዊውን ዓላማዎቹዋን ግብ ለማድረስና ከገጠሙዋት ችግሮች መላቀቅ እንድትችል እላይ
በጠቀስናቸው አማራጭ በማይገኝላቸው ጉዳዮች ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሥርነቀል
ውሳኔ እንዲያስተላልፍ
በማክበር እናሳስባለን።
4. ስብከተ ወንጌልን ስለ ማጠናከርና ስለ ማስፋፋት፤
በሕገ ቤተ ክርስቲያናችን እንደሚከተለው ተደንግጉዋል፤
አንቀጽ 7 ቁጥር 7 “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት በአገር ውስጥና በውጭ አገር እንዲስፋፋ
ያደርጋል።”
ነገር ግን፤ ከላይ በተጠቀሰው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መመሪያ መሠረት የተወሰደው እርምጃ እጅግ አነስተኛ ነው።
እንደሚታወቀው፤ በአገራችን በኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናንና ምእመናት ስለ እምነታቸው በቂ
ትምሕርት ስለማያገኙ በብዛት ወደ ሌሎች እምነቶች እየፈለሱ በመሔዳቸው የቤተ ክርስቲያናችን እምነት
ተከታዮች ቁጥር እየቀነሰ ከመሔዱም በላይ በተለይ በገጠሩ የሚኖሩት ምእመናን ስለ ወንጌልም ሆነ ስለ
እምነታችን ያላቸው ግንዛቤ እጅግ አነስተኛ መሆኑ የታወቀ ነው። በአንጻሩ፤ የሌሎች እምነት ተከታዮች ቁጥር
እየጨመረ መሔዱ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የሌላው እምነት ተከታይ እምነቱን እንዲቀበል በስልት ተምሮ
የተቀበለውን እምነት በጣፈጡ ቃላት ለእኛው እምነቱን ያስተማረው ለሌለውና ለማያውቀው ምእመን እየሰበከ
ባል ሚስቱን፤ ሚስት ባልዋን ሲያስኮበልሉ ይታያሉ። ከኢትዮጵያ ውጪ በመላው ዓለም ተሰራጭተው በሚገኙ
ኢትዮጵያውያን ጥረትና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ፕሮግራም በውጭ ሐገሮች በብዛት
3
በተቁዋቁዋሙት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ካሕናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን እምነት በይፋ ለሌሎች ዜጎች
ስለማያስተምሩ ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የሌሎች ዜጎች ምእመናንንና ምእመናትን አባል ማድረግ ስትችል
የሚያስተምራቸው ስለሌለ እምነታችንን የተቀበሉ የውጭ ሐገር ዜጎች በጣም ጥቂት ናቸው። ስለሆነም፤ ከላይ
የተጠቀሰውን ችግር ቀስ በቀስ ማስወገድና ስብከተ ወንጌልን በስፋት እያሰራጩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች
ምእመናንና ምእመናትን ቁጥር ማብዛት የሚቻልበት ዘዴዎች በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ዘንድ የሚታወቁ ቢሆንም
ለመጠቆም ያህል የወንጌል መልእክተኞቻችን በሐገራችን ቁዋንቁዋዎችና በሌሎች ዜጎች ልዩ ልዩ ቁዋንቁዋዎች
በብዛት ማሠልጠንና እንደ ሌሎቹ እምነት አስተማሪዎች በየገጠሩ በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በየመንደሩ
እየተዘዋወሩ እንዲያስተምሩ ማድረግ፤ በመጻሕፍት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የሚነበቡ በራሪ ወረቀቶችን በልዩ ልዩ
ቁዋንቁዋዎች በብዛት እያዘጋጁ ማሰራጨት፤ በመገናኛ ብዙኅን ማለት በሬዲዮ፤ በቴሌቪዥን፤ በድረገጽና
በመሳሰሉት ትምሕርተ ወንጌልን፤ እምነታችንና ቀኖናችንን ማሰራጨት ስለሚቻል ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ አስፈላጊና
አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርጎ አመርቂ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ እናምናለን።
5. ደብሮችንና ገዳሞችን ስለ መርዳት፤
ከደርግ ዘመን ጀምሮ፤ ቤተክርስቲያናችን አብዛኛውን ንብረቷን ስለ ተዘረፈች ብዙ ደብሮችና ገዳሞች ችግር ላይ
ይገኛሉ። በብክነት ምክንያት፤ ከምእመናን የሚገኘውም በትክክሉ እንዲደርሳቸው አልተደረገም። በተከሠተው
መናቆር ምክንያትም፤ ውጪ ሐገሮች ያሉት ምእመናንም በሚችሉት መርዳት አልቻሉም። በተጨማሪም፤ እጅግ
አሳሳቢ ሆኖ የቆየው፤ ታሪካዊው የኢየሩሳሌሙ “ዴር ሡልጣን” (1) ገዳማችን የሚያስፈልገው ጥገና
ስላልተከናወነለት የመፍረስ አደጋ ላይ ነው። ስለዚህ፤ ቤተክርሲቲያናችን ካላት ገቢ፤ ደብሮችና ገዳሞች ተገቢውን
ድርሻቸውን እንዲያገኙ፤ ለዘለቄታውም ራሳቸውን እንዲችሉ ተገቢ በሆነ ሥልት እንዲጠቀሙና፤ ከውጪም
የሚገኘው ድጋፍ እንዲዳብር፤ የእሥራኤል መንግሥትም የኢየሩሳሌም ገዳማችን እንዲጠገን ፈቃዱ እንዲሆን፤
ቅዱስ ሲኖዶሱ ተገቢ የሆነ ጠንካራ ሥልት አዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲያውል በማክበር እናሳስባለን።
6. ስለ ትምህርት ማስፋፋትና ማጠናከር፤
ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ የወጣው ሕገ ቤተክርስቲያን፤ አንቀጽ 7 ስለ “የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣንና ተግባር”½
እንደሚከተለው ደንግጓል፤
ቁጥር 8፤ “የክርስቶስን ወንጌለ መንግሥትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ያስተምራል ያስፋፋል።”
ሆኖም፤ ቤተክርስቲያናችንን ካጋጠሟት እጅግ ከባድ ችግሮች አንዱ የአብነት ትምሕርት ቤቶች መዳከም ነው።
ቀድሞም ሆነ በአሁኑ ዘመን፤ የአብያተ ክርስቲያናችን ሕልውና መሠረት የአብነት ትምህርት ቤቶች መሆናቸው
ይታወቃል። ገዳማትንና አድባራትን የሚያገለግሉት ካህናት ምንጭ የአብነት ትምህርት ቤቶች ናቸው። የብፁአን
ወቅዱሳን ፓትሪያርኮች፤ የብፁአን ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ምንጭ የአብነት ትምሕርት ቤቶች ናቸው።ስለዚህ
የእነዚህ አብነት ትምህርት ቤቶች መዳከም ማለት የቤተ ክርስቲያን መዳከም ማለት መሆኑ እውነት ነው።
ከአስተዳደር ችግሩ በተጨማሪ የገጠሬው ምእመን በከፋ ድሕነት ስለሚሰቃይ ለቆሎ ተማሪውና ለአስተማሪው
የተለመደ ቸርነቱን ሊያበረክትለት አልቻለም። ለጋሽ የነበረው የኢትዮጵያ ገበሬ ተመጽዋች በመሆኑ የቆሎ
ተማሪዎችና መምህራኖቻቸው የእለት ጉርሳቸውንና የዓመት ልብሳቸውን ከገበሬው በምጽዋት ማግኘት ስላልቻሉ
ወደየከተማው በመሰደድ ላይ ናቸው። በዚህ ምክንያት፤ የቤተክርስቲያናችን ምንጭ የሆኑት የአብነት ትምሕርት
ቤቶች አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ውጪ ሀገሮች ላሉት ምእመናንም ተገቢ የሆኑ የሥልጠና ማእከሎች
(1) ማሕበራችን ስለ ታሪካዊው የኢየሩሳሌም ገዳማችን ለእስራኤል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የሚያቀርበውን
አቤቱታ በዓለምአቀፍ
ደረጃ በማስፈረም ላይ መሆኑን የሚያሳየውንና ያሰራጨውንም መግለጪያ በድረገጹ
በwww.eotcipc.org½ይመልከቱ።
4
ስላልተቋቋሙላቸው በቤተክርስቲያናችን ትምሕርት የጠለቀ እውቀት ሊያገኙ አልቻሉም። ስለዚህ፤ የአብነት
ት/ቤቶች እንዲጠናከሩና ውጪ ሐገሮችም የቤተክርስቲያናችን ት/ቤቶች እንዲቋቋሙ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለጉዳዩ ልዩ
ትኩረት በመስጠት በባለሙያዎች ጥናት ላይ የተመሠረት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያስገኝለት በትሕትና እናሳስባለን።
7. አክራሪዎች ስላደረሱት ጥቃት፤
ቤተክርስቲያናችንን ካጋጠሟት እጅግ መራርና አስቆጪ ጥቃቶች አንደኛው አክራሪ እስላሞች ካሕናትንና
ምእመናንን አሰቃቂ በሆነ መንገድ መጨፍጨፋቸው፤ ደብሮችንና ገዳሞችን ማቃጠላቸውና ከጠላት ሐገሮች
በሚያገኙት ገንዘብ ቤተክርስቲያናችንን በብዙ መንገድ መፈታተናቸውን መቀጠላቸው ነው። በተለይ በ1997 እና
1998 ዓ/ም ከምሥራቅ ሐረርጌ ክፍለ ሐገር ጋራሙለታ ጀምሮ በምዕራብ እስከ ኢልባቦርና ከፋ ክፍላተ ሐገራት
ባሉት አገሮች በባሌና አርሲ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የፈረሱና የተቃጠሉ፤ ብዙ ካህናት የተሰየፉ፤ እንደ እንስሳ
የተቀሉ፤ ተገድደው የሰለሙ መሆናቸው ያደባባይ ምሥጢር ነው። ስለዚህ ሁሉ ግፍ፤ በቤተክርስቲያናችን አመራር
ምን እንደ ተከናወነና ምን ክትትል በመደረግም ላይ እንዳለ የሚታወቅ ነገር የለም። የተከናወነው አሰቃቂ ግፍ
ተጀመረ እንጂ ያበቃለት አለመሆኑን፤ እንዲያውም የባሰ ጥቃት ሊከሰት እንደሚችል አውቆ፤ ነቅቶ እንዲጠብቅ
ለቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን በሰፊው ማስገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ይህን ከባድ ጉዳይ
በዝርዝር በማጥናት ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም ቤተክርስቲያናችን ለራሷ ብቁ፤ ለዘመኑ አመች
የሆነ ሕጋዊ መከላከያ እንዲኖራት ለማድረግ የሚያስችል ሥልት አዘጋጅቶ ሥራ ላይ ማዋል የሚያስፈልግ መሆኑን
በአክብሮት እናሳስባለን።
8. ስለ ድሕነት፤
ከላይ በተጠቀሰው ሕገ ቤተክርስቲያን፤ አንቀጽ 6 ቁጥር 6 አንደኛው የቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማ እንደሚከተለው
ተገልጿል፤
“የሰው ዘር ሁሉ ከርሃብ፤ ከእርዛት፤ ከበሽታና ከድንቁርና ተላቆ በሰላምና በአንድነት በመተሳሰብና
በመረዳዳት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖር ማስተማርና መጸለይ፤”
የሐገራችን ሕዝብ እጅግ በከፋ የድሕነት አረንቋ ፍዳውን እያየ መሆኑ የታወቀ ነው። ቤተክርስቲያናችንንም
ለእምነቱ መጠጊያ፤ ለረሐቡም ማስታገሺያ እንድትሆንለት ይፈልጋል። በዚህ ረገድ፤ ቤተክርስቲያናችን ለደኸየውና
ለታረዘው ወገናችን በበለጠ ሁኔታ ደራሽ እንድትሆን ተገቢ ሥልት እንዲቀየስና ሥራ ላይ እንዲውል፤ ቅዱስ
ሲኖዶሱ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ በትሕትና እናሳስባለን።
9. መደምደሚያ፤
ከላይ የዘረዘርናቸው ጉዳዮች የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኩዋይ ትኩረት የሚገባቸው መሆኑ ቢታወቅም፤ ምእመናን
መፍትሔ የሚሹባቸው ሌሎች ችግሮችም አሉ። ከነዚህ ውስጥ ጥቂቱን ለመጥቀስ፤ (ሀ)ቃለአዋዲውን
ስለ
ማሻሻል፤ (ለ) መጠናት ስለሚገባቸው ድርሳናት፤ ገድላት፤ ውዳሴያትና ታምራት፤ (ሐ) የምእመናትን ተሳትፎ ስለ
ማጠናከር፤ (መ) ቅዱስ ቁርባኑን ባለመቀበል፤ አብዛኛዎቹ ምእመናንና ምእመናት በቅዳሴያችን በግልጽ እንደ
ተቀመጠው፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አፍራሾች ሆነን ስለ መገኘታችን፤ ወዘተ ይገኙበታል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ መልካም ፈቃዱ ሆኖ፤ ከላይ የዘረዘርናቸውን ጉዳዮች በጥሞና ተመልክቶ አስፈላጊውን መመሪያ
እንዲሰጥና ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት የሰፈነባት፤ በተሟላ ሥልት፤ አቅድና፤ ፕሮግራም
የምትንቀሳቀስ፤ በቅልጥፍና፤ በግልጽነትና በአስተማማኝ ቁጥጥር የምትሠራ፤ ስብከቷና ትምሕርቷ ለዓለም ሕዝብ
ሁሉ የሚዳረስ፤ የማትደፈር፤ ራሷን የቻለች፤ ምእመኖቿም በእምነታቸው የጸኑ የብዙ ሐገሮች ዜጎች እንዲሆኑ
እንዲያደርግ የሁልጊዜም ጸሎታችን ነው።
ቅዱስ ሲኖዶሱ፤ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት፤ ባሁኑ ጊዜ በቤተክርስቲያናችን ላይ የተጋረጡትን ከባድ ችግሮች
በሚገባ እንዲወጣ ለቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ተንበርክከን እንጸልያለን። አሜን።
እጅግ ከፍ ካለ የአክብሮት ሰላምታ ጋር፤
ኢዮኤል ነጋ
የማሕበሩ ዋና ጸሐፊ።

No comments:

Post a Comment